የትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ 4ኛ ጠቅላላ ጉባዔ የአቋም መግለጫ
ሙስና እጅግ አስከፊና አስነዋሪ ድርጊት መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ በሀገራችን የቆየ ባህልና የሕብረተሰቡ አመለካከት ሙስና የተወገዘ ተግባር ከመሆኑም ሌላ ሙሰኞችም ከፍተኛ የሕግ ቅጣት ሲፈጸምባቸው እንደነበርና በተግባራቸውም በማኀበራዊ ኑሮ ተገልለው አንገታቸውን እስከመድፋት ይደርሱ ነበር፡፡
ይሆንና በአሁኑ ወቅት በአገራችን የሙስና ይዘትና ስፋት እጅግ እየተስፋፋና ሥር እየሰደደ በመጓዝ ላይ ይገኛል፡፡
ድርጊቱ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና በግል ድርጅቶች መልኩንና ይዘቱን እየቀያየረ እንደወረርሽኝ እየተስፋፋ ይገኛል፡፡ በከተማም ሆነ በገጠር በአፋጣኝ እየተንሰራፋ ነው፡፡
በዚህ መሠረትም በአሁኑ ወቅት ጉቦ መስጠትም ሆነ መቀበል ነውር የማይሆንበት ደረጃ ላይ የደረሰ ይመስላል፡፡ ጉዳዩቹን በሕግ በተቀመጠ አግባብ ከመፈጸምና ከማስፈጸም ይልቅ በአቋራጭ በሙስና መፈጸምና ማስፈፀም እንደ ባህል እየተወሰደ ከመሆኑም በላይ ሙስኞችም እንደነውረኛና እንደወንጀለኛ ተቆጥረው ሲወገዙና በህብረተሰቡም ሲገለሉ አይታይም፡፡
በየመሥሪያ ቤቱ ያሉትን የአሠራር ክፍተቶችን በመጠቀም ከሕግ ተጠያቂነት ለመዳን የተራቀቁና አገርንና ሕዝብን የሚጐዱ ወንጀሎችን ሲፈጽሙ ይገኛሉ፡፡ በዚሁ ረገድ በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ የተፈጸሙትን ትላልቅ የሙስና ድርጊቶችን ለአብነት መጥቀሱ ችግሩ ምን የህል በተራቀቀና በተወሳሰበ እንዲሁም በተቀናጀ መንገድ እየተፈጸመ መሆኑን መገንዘብ ይቻል፡፡
ባሌስትራን ወርቅ በማስመሰል ለብሔራዊ ባንክ የተሸጠበትን ሁኔታና በአዲስ አበባ ከተማ የሕገ ወጥ የመሬት አሰጣጥን እና ሌሎችንም በየጊዜው እየተፈፀሙ ያሉትን ሕገወጥ ድርጊቶች መመልከቱ በቂ ማስረጃ ነው፡፡
በመንግሥትና በግል ድርጅቶች እንዲሁም በቀበሌና በሌሎችም የአስተዳደር እርከኖች ያለው የአሠራርና የአፈጻጸም ሂደትም ሙሉ ለሙሉ ከሙስና የፀዳ ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡
በመሆኑም ሙስና ካልተገታ በወቅቱ የተፈጠረውን የኑሮ ውድነት እያባባሰና በተለይም የድሃውን የህብረተሰብ ክፍል የመኖር ህልውና አጠያያቂ ደረጃ ላይ የሚያደርሰው ይሆናል፡፡
የሙስና መስፋፋት በልማት፣ በፍትህና በዲሞክራሲያዊ ሂደት ላይም ከፍተኛ ጋሬጣ ከመሆኑም ሌላ ሕዝቡ በመንግሥትና በሕግ ላይ አመኔታ እንዳይኖረው የሚያደርግ ነው፡፡
ስለሆነም ሙስናን ለመታገልና በአገራችን የሕግ የበላይነትና ተጠያቂነት እንዲሰፍን የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት የተቋቋመው የትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ ጠቅላላ ጉባዔ ግንቦት 2 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም በግዮን ሆቴል በካሄደው ስብሰባ በአገራችን እየተስፋፋ በሚገኘው የሙስሃ ድርጊትና ችግሩን ለማስወገድ ስለሚቻልበት ሁኔታ በጥልቀት በመወያየት ከዚህ የሚከተለውን የአቋም መግለጫ አውጥቷል፡፡
- መንግሥትን በሚመለከት
መንግሥት ሙስናን ለመታገልና ለማጥፋት እንዲቻል የፀረ-ሙስና ኮሚሽንን በሕግ እንዲቋቋም ማድረጉና ኮሚሽኑንም ለማደራጀት ያደረጋቸው ጥረቶች የሚበረታቱ ቢሆንም አሁንም ሙስና እየተስፋፋና እየጨመረ እንዲሁም መልኩንና ይዘቱን እየቀየረ በሕዝብና በመንግሥት ንብረት ላይ ምዝበራ እየተፈጸመ ይገኛል፡፡ ችግሩን ለመታገል በመንግሥት በኩል ተጨማሪ እርምጃዎች መወሰድ አለባቸው ብለን እናምናለን፡፡ በመሆኑም መንግስት፡
- ሙስናን ለመታገልና ለማጥፋት የሚያስችሉ ተጨማሪ ሕጐችን እንዲያወጣ፣
- ሙስናን ለመዋጋት በየደረጃው የተቋቋሙት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ለተቋቋመለት ዓላማ ታማኝ ሆነው እንዲያገለግሉ አስፍላጊውን ትምህርት እንዲያገኝና ክትትልና ቁጥጥርም እንዲያደርግባቸው፣
- በየደረጃው የሚሾሙ የመንግሥት ኃላፊዎች በጥንቃቄና በብቃታቸው እንዲመረጡ እንዲያደርግ፣
- ተጠያቂነትና ግልጽነት የሕግ የበላይነት የሰፈነበት አሠራር እንዲዘረጋ እንዲያደርግ፣
- በሙሰኞች ላይ አፋጣኝ የሆነ የሕግ እርምጃ እንዲወሰድ እንጠይቃለን፣
- የግል ድርጅቶችን በሚመለከት
አንዳንድ የግል ድርጅቶች በተለይም በንግድ ሥራ ላይ የተሠማሩ ዜጐች ጉዳያቸውን በአቋራጭ ለማስፈጸም ጉቦ ይሰጣሉ ይህም ድርጊት ሙስና ከመሆኑም በላይ ሙስናን በማስፋፋትና በማበረታታት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ተደጋግሞ እንደተነገረውም ጉቦ የሚሰጥ ከሌለ ጉቦኛ አይኖርም ነውና የግል ድርጅቶችና የንግዱ ሕብረተሰብ በመሆኑም፡-
- ሙስናን እንዲያወግዙና ከፍተኛ ወንጀልና ነውረኛ ተግባር መሆኑን እንዲገነዘቡ፤
- ሙስናን ለመታገል ከሚሠሩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በቅንጅት እንዲንቀሳቀሱ፤
- ለሙስና በር የሚከፍቱ አሠራሮችና ፖሊሲዎች እንዲስተካከሉ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የመንግሥት መ/ቤቶች ሃሳብ እንዲያቀርቡና ግፊትም እንዲያደርጉ፤
- በንግድ ምክር ቤቶችና በአሠሪ ማኀበራት አማካኝነት ፀረ-ሙስና ትግል እንዲያደርጉ፤
- ሙስናን በሚመለከት በየድርጅቶቻቸው የስነ-ምግባር መመሪያ(Code of Conduct) እንዲያወጡ እንጠይቃለን፡፡
- የሲቪል ሕብረተሰብን በሚመለከት
ሙስና የትኛውም ቦታና ደረጃ የሚፈጸም ድርጊት በመሆኑ ለማጥፋትም የመላውን ሕብረተሰቡ ተሳትፎና ትብብር የሚጠይቅ ነው፡፡ አብዛኛው የሙስና ተግባር ከህብረተሰቡ የተደበቀና የተሠወረ አይደለም በመሆኑም፡-
- ህብረተሰቡ በየትኛውም ቦታና ደረጃ የሚከሰቱ የሙስና ድርጊቶችን እንዲያጋልጥና ለሕጋዊ አካል እንዲጠቁም፣
- ጉዳዩን በጉቦ ለማስፈጸም ከመሯሯጥ ይልቅ በሕግ አግባብ ብቻ ለማስወሰን በጽናት እንዲታገሉ፣
- ጉቦ መስጠትንና መቀበልን እንዲያወግዙ፣
- በቀበሌ እስከ ላይኛው አካል ድረስ በተዋረድ የተቋቋሙት የመንግስት አካላት ሥራቸውን በአግባቡ መሥራታቸውን እንዲከታተሉና እንዲገመገሙም እንዲያደርጉ፣
- በሕብረተሰቡ ተቋቋሙ ዕድሮች፣ የሙያና የሠራተኛ ማኀበራት ሙስናን ለመታገልና የሕግ የበላይነትን ለማስፈን ለአባሎቻቸው ትምህርት እንዲሰጡ፣
- መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም ሙስናን ለመታገል በሚደረገው ትግል ቀጥተኛ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪያችንን እናቀርባለን
- የምርምርና የትምህርት ተቋማትን በሚመለከት
ሙስናን ለመታገል ሙስኞችን በሕግ መጠየቅ አግባብ ቢሆንም በዋነኝነት መፍትሄ ሊሆን የሚችለው ግን የሙስናን አስከፊነት በሚመለከት ትምህርት በመስጠቱ ላይ መሆን ይገባዋል በመሆኑም፡-
- በየደረጃው የሚገኙ የትምህርት ተቋማት የወደፊቱን አገር ተረካቢ ወጣት ትውልድ በጥሩ ሥነ-ምግባር አንጾ ለማውጣት እንዲቻል የሙስናን አስከፊነትና በሀገር ላይም የሚያደርሰውን ችግር ለተማሪዎች እንዲያስተምሩ፣
- ሙስና በሀገር ዕድገትና በህብረተሰቡ ኑሮ ላይ የሚያስከትለውን አደጋ የሚያሳዩ የምርምና የጥናት ጽሑፎችን እንዲያዘጋጅና እንዲያሠራጩ፣
- ሙስናን በምንም መልኩ ቢሆን የሚሸከም ትውልድ እንዳይኖር ማስተማር ( Zero Tolerance) እንዲፈጠር እንጠይቃለን፡፡
- የሚዲያ ተቋማትን በሚመለከት
የሚዲያ ተቋማት ከተመሠረቱበት ዓላማና በህብረተሰብ ካላቸው ተደማጭነት አኳያ የሙስናን አስከፊነት በማስተማር ከፍተኛ ድርሻ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በመሆኑም፡-
- የመንግሥትም ሆነ የግል ሚዲያዎች ፀረ-ሙስና ትምህርት የሚሰጡበት ዓምድ እንዲከፍቱ፤
- የመንግሥትም ሆነ የግል መገናኛ ብዙሃን ሕብረተሰቡ በየጊዜው የሚከሰቱ የሙስና ወንጀሎችን እንዲያውቅና እንዲጠነቀቅም ትምህርት እንዲሰጡ፤
- በአጠቃላይ የመንግሥትም ሆነ የግል የሚዲያ ድርጅቶች ሙስና በመፈጸም የሚጠረጠሩ የመንግስትና የግል ድርጅቶችን በመከታተል በማስረጃ የተደገፉ ዘገባዎችን (Investigative Journalism) ለመንግስትና ለህብረተሰቡ እንዲያቀርቡ እንጠይቃለን፡፡
- ዓለም አቀፍ ማኀበረሰቡን በሚመለከት
በሀገራችን የሚሠሩ የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ አካላት ሙስናን ለመታገል በሚደረገው እንቅስቃሴ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ ግልጽ ነው፡፡ በመሆኑም፡-
- በየመሥሪያ ቤቱ ጉዳያቸውን ለማስፈጸም በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሕግን ተከትለው እንዲፈጽሙ፤
- ጉቦ የሚጠይቁ አካላት ቢያጋጥማቸው ለሚመለከተው የመንግሥት አካል ጥቆማ እንዲያቀርቡና ሙስናን ለመታገል በሚደረገው ትግል ተባባሪ እንዲሆኑና በፀረ-ሙስና ትግል ለተሠማሩ መንግሥትና መንግስታዊ ላልሆኑ ተቋማት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ እንጠይቃለን፡፡
በመጨረሻም የአቋም መግለጫው ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት በሙሉ በአድራሻቸው እዲላክ በመወሰን ጉባዔው ስብሰባውን አጠናቋል፡፡
|