መግቢያ | ስለአኛ | አድራሻ

   
 

ትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ ጠቅላላ ጉባዔውን አካሄደ

ትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ ጠቅላላ ጉባዔውን ግንቦት 2/2000 ዓ.ም ለግማሽ ቀን አካሂዷል፡፡ በግዮን ሆቴል በተካሄደው ስብሰባ የተገኙት አባላት በሦስት አጀንዳዎች ላይ ውይይት አካሂደዋል፡፡ እነዚህ አጀንዳዎች አመታዊ የሥራ አፈጻጸም ሪፓርት፣ የ1999 ዓ.ም ኦዲት ሪፓርት እና የድርጅቱ ረቂቅ የአባላት መመልመያ ፖሊሲ ናቸው፡፡ ጉባዔው በመጀመሪያዎቹ ሁለት ሪፖርቶች ላይ ጠለቅ ያለ ውይይት ከአካሄደ በኋላ አጽድቋቸዋል፡፡ በተመሣሣይ መልኩ ጉባዔው በአባላት የመመልመያ ፖሊሲ ላይ ውይይት ካደረገና አንዳንድ ማስተካከያዎችን ካደረገ በኋላ ፖሊሲውን በሙሉ ድምፅ አፅድቋል፡፡

በሌላ በኩል ባሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ በተደጋጋሚ እየተስተዋሉ ያሉትን የሙስና ቅሌቶችና የስነ-ምግባር መውረድ ከግምት ውስጥ ያስገባው ጉባዔ የአቋም መግለጫ በማውጣት መግለጫው ለመንግስት፣ መንግስታዊ ላልሆኑ ድርጅቶችና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት እንዲደርሳቸው ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

“ሙስናና የህዝብ አገልግሎት አሰጣጥ በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ የፓናል ውይይትተካሄደ

ትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ ከፌደራል የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ጋር በመተባበር “ሙስናና የህዝብ አገልግሎት አሰጣጥ፣ ጥቂት ዳሰሳዎች በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ” በሚል ርዕስ ያዘጋጀው የፓናል ውይይት ሰኔ 26 ቀን 2000 ዓ.ም በግዮን ሆቴል ተካሂዷል፡፡

የፓናል ውይይቱ አላማ ከብዙ በጥቂቱ የሚከተለው ነው፡፡ 

  1. በአንዳንድ ለሙስና ተጋላጭ የሆኑ የህዝብ አገልግሎት አካባቢዎች ላይ ለመወያየትና ግንዛቤን ለማዳበር፣
  2. ከሙስናና ከህዝባዊ አገልግሎት አሰጣጥ ጉዳዩች ጋር በተያያዘ መረጃ ለመለዋወጥና ልምድ ለመጋራት፣
  3. ልዩ ልዩ የመንግስት መ/ቤቶችና አጋር ድርጅቶች ከሚያከውኗቸው ፕሮግራሞችና እንቅስቃሴዎች በተጓዳኝ ለሙስና ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ ለማበረታታት፣
  4. ሙስናን በመዋጋት ረገድ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ዘንድ የጋራ መግባባት እንዲፈጠርና የሀላፊነት ስሜት እንዲዳብር፣
  5. ሙስና የብሔራዊ ልማት ጠንቅ እንዳይሆን ሊከላከሉ የሚችሉ መፍትሄዎችና የአሰራር ዘዴዎችን ለማስገኘት
  6. የሙስና ድርጊቶችን ለይቶ ለማውጣትና ህዝባዊ አገልግሎት አሰጣጥን ሊነኩ የሚችሉ ተቋማዊና ህጋዊ ክፍተቶች ላይ ለመወያየት ናቸው፡፡

የትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር፣ አቶ ኢያሱ ይመር ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር በሙስና ዙሪያ ግንዛቤን ከፍ ለማድረግ ታስቦ የሚካሄደው የፓናል ውይይት የተለያየ ልምድና ተሞክሮ ያላቸውን ባለሙያዎችና ግለሰቦች በአንድ ላይ በማገናኘት ሀሳብና ልምድ ለመለዋወጥ እንደሚረዳ ጠቅሰው፣ ይህም ያሉትን ችግሮች ለይቶ ለማወቅና በአገልግሎት አስጣጥ ውስጥ ያሉትን ሙስናዎች ለመግታት የሚረዱ ተጨባጭ የመፍትሄ ሀሳቦች ለማስገኘት ጠቀሜታው የጐላ እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡ በመጨረሻም ተሳታፊዎቹ የተለያየ ልምዳቸውን ለማካፈል በፓናል ውይይቱ ላይ ሰለተገኙ አመስግነዋል፡፡

በመቀጠልም አቶ ዓሊ ሱሌይማን የፌደራል ሰነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር  ንግግር አድረገዋል፡፡ አቶ አሊ በሲቪል ሰርቪስ ውስጥ የሚስተዋሉትን የሙስና ጥሰቶችና ድርጊቶች ለማስወገድ አዳዲስ አሠራሮችን ተግባራዊ ለማድረግ የተደረገው ጥረት አበረታች ቢሆንም በሀገራችን ከሚታየው መጠነ ሰፊ የልማት እንቅስቃሴ አንጻር ብዙ መሰራት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

በተለይም የአገልግሎት አድማሳቸው ሰፊ የሆነና ከቴሌኮሚኒኬሽን ጋር የተያየዙ ሥራዎችን የሚያከናውኑ፣ ከሀይል አቅርቦት ጋር ግኑኝነት ያላቸው ድርጅቶች፣ የፋይናንስ እና የህክምና ተቋማት፣ ገቢ ሰብሳቢ መ/ቤቶች፣ ፈቃድ ሰጪ ተቋማት፣ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩ እና የመሳሰሉት ካለባቸው ሀላፊነት አንጻር የአግልግሎት አሰጣጣቸውን ፈጣን፣ ቀልጣፋና ከሙስና እንዲሁም ከብልሹ ሥነ ምግባር የራቀ እንዲሆን የማድረግ ትልቅ አላፊነት አለባቸው ብለዋል፡፡

አቶ አሊ እሳቸው የሚመሩት ኮሚሽን ሙስናን ለመከላከልና ለመዋጋት የስልጣን ክልሉ በመንግሥት መ/ቤቶች እና የልማት ድርጅቶች አካባቢ በመሆኑ ትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ በግል ተቋማት እና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች አካባቢ የሚፈፀመውን የሙስና ድርጊት ለመግታት አድማሱን አስፍቶ  ሊንቀሳቀስ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በፓናል ውይይቱ ላይ ከሙስና ጋር የሚያያዝ ጭብጥ ያላቸው ሦስት የጥናት ወረቀቶች በአቶ ጋርቢስ ኮራጂያን፣ በዶ/ር ያይራድ አስናቀ እና በአቶ በዛብህ ገ/የስ ቀርበዋል፡፡ አቶ ሀይለሚካኤል አበራ፣ የሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ ፕሬዚዳንት ውይይቱን መርተዋል፡፡

የጥናት ጽሑፎቹን ተከትሎ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ከተሳታፊዎች ቀርበው ጥናቱን ባቀረቡ ባለሙያዎች ሰፋ ያለ መልስና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

በፓናል ውይይቱ የተለያዩ ጉዳዩች የሚመለከታቸው አካላትና ግለሰቦች ተገኝተዋል፡፡ እነዚህም ታዋቂ ግለሰቦች፣ የመንግስት ሀላፊዎችና ሠራተኞች፣ ባለሙያዎች፣ ምሁራን፣ ከግል ዘርፍ፣ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶችና ከሚዲያ የተወከሉ ግለሰቦችን ያካትታል፡፡

የዓለም የሙስና ሪፖርት ይፋ ሆነ

ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል “Global Corruption Report” በሚል ርዕስ በየአመቱ የሚያወጣው የአለም የሙስና ሪፖርት “ሙስና በውሀ ዘርፍ” በሚለው ጭብጥ ላይ በማተኮር ሰኔ 18/2000 ዓ.ም ይፋ ሆኗል፡፡ የሪፖርቱ ዋና መልዕክት “በውሀው ዘርፍ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱትን አያሌ የሙስና ድርጊቶች ትርጉም ባለው መንገድ ለማስወገድ ባለድርሻ አካላትን ማንቀሳቀስ አስፊላጊ ነው” የሚል ነው፡፡

ከዚህም ሌላ ሪፖርቱ በ1999 ዓ.ም 18ዐ ሀገራትን ያካተተ የሙስና ምልከታ (Corruption Perception Index) ይዞ ወጥቷል፡፡ በህዝባዊ ዘርፍ ውስጥ ያሉትን የሙስና መጠኖች ከንግዱ ህብረተሰብ፣ ከተንታኞች እንዲሁም ከዜጐች እይታ አንጻር የሚያትተው ይህ ምልከታ በሪፖርቱ ውስጥ በተካተቱት አብዛኞቹ ሀገሮች ያለው የሙስና ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ይጠቅሳል፡፡ እነዚህም ሀገሮች ኢትዮጵያን ጨምሮ በአለም ላይ ያሉ ድሀ ሀገሮችን የተካተቱበት ነው፡፡

ትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ የሬድዮ ፕሮግራም ጀመረ

ትንስፓረንሲ ኢትዮጵያ ከሚያዚያ 12 ቀን 2000 ዓ.ም ጀምሮ በሙስና ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሳምንታዊ የሬዲዮ ፕሮግራሞ ማስተላለፍ ጀምሯል፡፡ ፕሮግራሙ በኤፍ ኤም 98.1 በየሳምንቱ እሁድ ከ11 ሰዓት እሰከ 11፡30 ይተላለፋል፡፡

የፕሮግራሙ አጠቃላይ አላማ ስለሙስና ምንነት፣ መገለጫውና የሚያስከትለውን ጉዳት ለህዝቡ ለማሳወቅና ሙስናን የማይታገስ ህብረተሰብ በሀገሪቱ ውስጥ ለመፍጠር፡ በሚደረገው ጥረት አስተዋፅኦ ለማበርከት ነው፡፡ በተጨማሪም ፕሮግራሙ ሕዝቡ፣ መንግስት፣ የግሉ ዘርፍ እና ሲቪል ማኀበራት በሙስና ላይ ያላቸውን ሀሳብ የሚያንጸባርቁበትና የሚያንሸራሽሩበት የውይይት መድረክ ይሆናል ተብሎ ይታሰባል፡፡

ትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ በዚህ አጋጣሚ አድማጮች ሳምንታዊ ፕሮግራሙን እንዲከታተሉና አስተያየት መስጠት በሚፈልጉት ጉዳይ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ይጋብዛል፡፡

 
Copy right © 2008 Transparency Ethiopia