መግቢያ | ስለአኛ | አድራሻ

   
 

ትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ በመንግስት፣ በግል እንዲሁም በሲቪል ማኀበራት ውስጥ የሚታዩትን ዘርፈ ብዙ የሙስና ችግሮች ለመዋጋት ባለው የስራ ድርሻና ሀላፊነት መሠረት የሚከተሉትን አራት (4) ዓበይት ተግባራት ያከናውናል፡፡ እነዚህም፡-

  1. የተቋም ግንባታ
  2. ቅንጅትና ጥምረት ምስረታ (Networking and Coalition Building)
  3. ግንዛቤ ማዳበሪያ ስልጠናና ትምህርት
  4. ምርምርና ውትወታ (Research and Advocacy) ናቸው፡፡

1. የተቋም ግንባታ

በዚህ ስራ የሚታቀዱና የሚታሰቡ ስራዎችን ወደተግባር ለመለወጥ ቁልፍ መሣሪያው የአቅም ግንባታ ነው፡፡ የተቋም ግንባታ ስልጠና መስጠት፣ የጽህፈት ቤት ቢሮ መከራየትና መሠረታዊ ቁሳቁሶችን ማሟላት፣ የቢሮ ዕቃዎች ግዥ ማከናወን፣ የተቋሙን ድህረገጽ መረብ መዘርጋትና መረጃ ማስተላለፍ፣ ከሙስናና ከመልካም አስተዳደር ጋር የሚያያዙ ሰነዶችና ጽሑፎችን ያካተተ ቤተመጽሃፍት ማደራጀትና ለተጠቃሚዎች አገልግሎት መስጠት፣ የአባላት ምልመላ፣ ፈንድ ማሰባሰቢያ እንቅስቃሴዎች የዚህ ፕሮግራም አካል ናቸው፡፡

የትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ አባላት የሚሳተፉበት ልዩ ልዩ ስብሰባዎች ለእርስ በርስ መማማሪያ ጠቃሚ መድረኮች ሲሆኑ፣ እነዚህ ስብሰባዎች ለአባላቶቹ ትምህርት ይሰጣሉ ተብለው በሚታሰቡ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደርጋሉ፡፡ አለም አቀፍ ኮንፍረንሶችን ማዘጋጀት የትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል አለም አቀፍና ክልላዊ አባላትን ለመሳብ እንደአንድ አማራጭ መንገድ የሚወሰድ ሲሆን ሙስናን ለመዋጋትና ግልጽነትን ለማስፈን የሚረዱ የየሃገሮችን ልምድና ተሞክሮ ለመለዋወጥና ለመጋራት የሚያስችሉ ጠቃሚ መድረኮች ናቸው፡፡

2.  ቅንጅትና ጥምረት ምስረታ

እንደ ትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ ዕምነት የፀረ ሙስናው ትግል ውጤታማ ከሚሆንባቸው መንገዶች አንደኛው የቅንጅትና ጥምረት ምስረታ ነው፡፡ የዚህ ፕሮግራም ዋና ትኩረት ተመሳሳይ እምነትና አስተሳሰብ ያላቸውን ግለሰቦች እና በመልካም አስተዳደር፣ በፀረ ሙስናና በሰብአዊ መብት ጉዳዮች ላይ የሚሰሩ ድርጅቶችን በአንድ አላማ ስር ለማሰባሰብ ነው፡፡ ትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ ድርጅቱ ግፊት መፍጠሪያና በፀረ ሙስናው ትግል አቅጣጫ አመላካች መሆን ይኖርበታል ብሎ ያምናል፡፡፡፡ በመሆኑም ከመንግስት፣ ከሲቪል ማኀበራትና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በጋራ መስራት የትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ ዋነኛ አጀንዳ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ እንደ ፌዴራል ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ከመሳሰሉ ተቋማት ጋር ጥሩ የስራ ግኑኝነት ለመፍጠር ተችሏል፡፡ በዚህ የተነሳ ሁለቱ ተቋማት በፀረ-ሙስና ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር በየሦስት ወሩ የሚካሄድ የፓናል ውይይት በጋራ ያዘጋጃሉ፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር ለፓርላማ አባላት ስልጠና ከመስጠት ጋር በተያያዘ አብሮ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡

በፌዴራል ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን አነሳሽነት በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ ስምንት የሚሆኑ ሲቪል ማኀበራት የፀረ-ሙስና የጋራ ጥምረት ፈጥረዋል፡፡ ይህ ጥምረት የተቋሞቹን አቅም ለማሳደግ፣ እንዲሁም በጋራ የሚመለከቷቸውን ጉዳዮችና አጀንዳዎች በጋራ ለማሰማት እንደሚጠቅም ይታመናል፡፡

ውትወታና የማሳመን ስራን በተመለከተ ትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ ሙስናን ባለበት ለመግታት የሚረዱ የስራ አካሄዶች፣ ፖሊሲዎች፣ መመሪያዎችና ደንቦች በስራ ላይ እንዲውሉ ውትወታና የመገፋፋት ስራ አከናውኗል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ መንግስት የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የአፍሪካ ህብረትን የፀረሙስና ድንጋጌዎች አጽድቆ ተግባራዊ እንዲያደርግ የሚያሳስብ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ተጽፏል፡፡ በሌላ በኩል የአፍሪካ የፓርላማ አባላት የፀረ-ሙስና ጥምረት በኢትዮጵያ የፓርማ አባላት አማካኝነት እንዲመሰረት ጥረት በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡ ትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ የትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ ቻፕተር እንደመሆኑ መጠን ከዚህ አለም አቀፍ ተቋም ጋር ጠንካራ ግኑኝነት መስርቷል፡፡ ከዚህም ባሻገር ኬንያን ከመሳሰሉ የአፍሪካ ቻፕተሮች ጋር የስራ ጉብኝት በማድረግ፣ በወርክሾፖችና ኮንፍረንሶች በመሳተፍ የልምድ ልውውጥ ይደረጋል፡፡

3. ግንዛቤ ማዳበሪያ ስልጠና እና ትምህርት

ትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ ዜጐች ግንዛቤያቸው እንዲያድግና የሙስና ድርጊቶችን ለመግታት በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው የሚያግዙ የተለየዩ ፕሮግራሞችን ያካሂዳል፡፡

እንደሚታወቀው የትምህርት ዋነኛ ግብ የባህሪ ለውጥ እንዲመጣ ማድረግ ነው፡፡ ሌላው ቢቀር ዜጐች ስለሙስና እና ስለጉቦ ጐጂነት እንዲያውቁ ማድረግ በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ እንዲሰጡ ይረዳቸዋል፡፡

እነዚህን አላማዎች ወደተግባር ለመለወጥ የተለያዩ የኮሚኒኬሽን ዘዴዎች በጥቅም ላይ፣ ይውላሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ ጠንካራ የውትወታ ስራ፣ የሚዲያ ቅስቀሳ ፣ የድህረ-ገጽ መረጃ፣ ህዝባዊ ትምህርቶች፣ ኮንፍራንሶች፣ የፓናል ውይይት፣ ድራማ እና ሲኒማ፣ ብሮሸሮች፣ በራሪ ጽሁፎችና የዜና መፍሔቶች ይገኙበታል፡፡ የትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ አባላት በሙስና ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ግንዛቤ ከፍ ማድረግም በዚህ ፕሮግራም ውስጥ የሚካተት ነው፡  ለተጨማሪ መረጃ

4. ምርምርና ውትወታ

ትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ የፀረ-ሙስና ትግሉ ያለበትን ደረጃ ለመገምገምና ለመከታተል የሚያገዙ ምርምሮችና ጥናቶች ያካሄዳል፡፡ በዚህ ረገድ ህዝቡ በሙስና ላይ ስላለው አመለካከት ለመገምገም የሚያስችል ጥናት ለማካሄድ እቅድ ተይዟል፡፡ ከዚህ አኳያ ጥናቱን የሚያካሄደው ድርጅት ተመርጦ ሥራውን ለመጀመር በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህም ሌላ በንግድ ዘርፍና በመንግስት ተቋሞች ውስጥ የሚታዩትን የሙስና ደረጃዎች ለማወቅ የሚያስችሉ ጥናቶች ይካሄዳሉ፡፡

እነዚህ ጥናቶች ሀገር አቀፍ ጥናት ለማካሄድ እንደመነሻ የሚያገለግሉ መረጃዎች ናቸው፡፡ በተጨማሪም በድርጅቱ ለሚካሄዱ ሌሎች ተግባሮች፣ ለምሳሌ፣ ህዝቡን ለማስተማር፣ ለውትወታና ቅስቀሳ ስራ፣ የተገኙ ስኬቶችንና ድክመቶችን ለመፈተሽ፣ እንዲሁም ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን ለመለየት እንደግብአት ያገለግላሉ፡፡ ከዚህም በላይ የተለየ ችግር  ያለባቸውን ቦታዎች ለመገምገምና የፀረ-ሙስና ንቅናቄው ያስገኘውን ለውጥ ለመከታተል ያግዛሉ፡፡

 
Copy right © 2008 Transparency Ethiopia