መግቢያ | ስለአኛ | አድራሻ

   
 

ትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ መንግስታዊ  ያልሆነ፣ ለትርፍ የማይንቀሳቀስ ሀገር በቀል ድርጅት ነው፡፡ ትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ ሙስና በሀገርና በወገን ላይ የሚያደርሰውን ማኀበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ለመከላከልና ለመቀነስ ተመሳሳይ አለማ ካላቸው ሲቪል ድርጅቶች፣ መንግስታዊ ተቋማት፣ አለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ከግሉ ዘርፍ፣ ከማዲያ አካላትና ከኀብረተሰቡ ጋር ጥምረት ፈጥሮ የሚንቀሳቀስ የፀረ-ሙስና ማኀበር ነው፡፡

ይህ ተቋም መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው አሰራር ሰፍኖ የህግ የበላይነት የተከበረበት፣ ጠንካራ የሆነ የፀረ-ሙስና ጥምረት የተፈጠረባት በአለም ላይ እንደምሳሌ የምትጠቀስ ኢትዮጵያ ማየት ግቡ ያደረገ ነው፡፡

ትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ ለማቋቋም መነሻ የሆነው የአለም አቀፍን የፀረ-ሙስና እንቅስቀሴ በተለያየ አጋጣሚ በመሳተፍ ከአለም አቀፍ ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል አመራሮች ጋር ጠንካራ ግኑኝነት መፍጠር በቻሉ ኢትዮጵያውያን አማካኝነት በቀረበ ሀሳብ ነው፡፡

በዚህ መሠረት ማኀበሩን ለመመስረት በተሰባሰቡ ዜጎች እንቅስቃሴ ተጀምሮ ጥር 23 እና 24 ቀን 1995 ዓ.ም በአፍሪካ ኢካኖሚ ኮሚሽን ስብሰባ አዳራሽ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች፣ ከግል ዘርፍ፣ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ከሠራተኛ ማኀበራት፣ ከትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ተወካዮችና ከታዋቂ ግለሰቦች የተወጣጡ ከ 300 በላይ ተሳታፊዎች በተገኙበት በተለያየ ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፍ እንዲቀርብና ውይይት እንዲካሄድበት ከተደረገ በኃላ በዚህ ህዝባዊ የፀረ-ሙስና ኮንፍረንስ የማኀበሩን ከፍተኛ አመራር አባላት በመምረጥ በይፋ ማኀበሩን ለመመስረት ተችሏል፡፡

የማኀበሩ ራዕይ
በሁሉም የኢኮኖሚ መስኮች ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲሰፍን፣ ህዝባዊ አገልግሎቶች በተቀመጡ መመሪያዎች መሰረት እንዲሰጡ፣የንግድ ልውውጦች የገበያ ህጐችና መመሪያዎችን ተከትለው እንደካሄዱ እና ኀብረተሰቡን ማዕከል ያደረገ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ የሀብት ክፍፍል በሙስና የማይጐዳበት ከሙስና ነፃ የሆነች ኢትዮጵያን እውን ማድረግ ነው፡፡

ተልዕኳችን
በመንግስት፣ በግል እና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ ያሉ ዘርፈ ብዙ የሙስና ችግሮችን መከላከልና በህዝባዊ ጉዳዩች መልካም አስተዳደርና ርዕቱነትን ማራመድ ነው፡፡

እሴቶቻችን
ፍትህ፣ ግልጽነት፣ ተጠያቂነት፣ ሰብአዊነት፣ ተአማኒነት ተቆርቋሪነትና ዲሞክራሲ፡፡

አጠቃላይ አላማችን
ሠፊ መሠረት ያለው ፀረ-ሙስና ጥምረት በመመሥረት ህዝባዊና ፖለቲካዊ ሀይሎች ሙስናን በጋራ እንዲዋጉ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ነው፡፡

ዝርዝር አላማዎቻችን

  1. ዜጐች ሕገ መንግስቱ ያጐናጸፋቸውን መብቶችና ግዴታዎችን ጠንቅቀው እንዲረዱና እንዲጠቀሙ ማሳወቅ፤
  2. ሕብረተሰቡ ከሙስና ነፃ የሆነ የባህሪይ ለውጥ እንዲያመጣ የሚያስችለው ባህል መፍጠር፤
  3. የግልጽነትና የተጠያቂነት ባህል በመንግሥት ኃላፊዎችና ማኀበረሰባዊ ተቋማት መሪዎች ዘንድ እንዲሰርፅ ሙሉ ጥረት ማድረግ፤
  4. የሙስና ወንጀሎችን ለመከላከል የሚያገለግሉ ሕጐችን በህብረተሰቡ ዘንድ በቀላሉ ተለይተው እንዲታወቁና እንዲሰርፁ ማድረግ፤
  5. የአመለካከት፣ የአስተሳሰብና የሞራል ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ጽሑፎችን በማዘጋጀት በኀብረተሰቡ ላይ የሚያደርሰውን ጉዳይ ለማጋለጥ የሚያስችል ሁኔታዎች መፍጠር፣ ማሠራጨትና ትምህርት መስጠት፤
  6. ሕፃናትና ወጣቶች በመልካም ሥርዓት፣ በግብረገብነትና በግልጽነት ታንፀው የሚያድጉባቸው ዘዴዎች መቀየስና ከወዲሁም ሙስና መዋጋት የሚያስችላቸውን ባሕል መፍጠር፤
  7. ከሚመለከታቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ጋር በመመካከርና በመተባበር የተለያዩ የሕግ ግንዛቤን የሚያዳብሩ ሴሚናሮችና ሲምፖዚየሞችን ማዘጋጀት፣
  8. በመንግሥት ሥራና በማህበራዊ አገልግሎት የተሰማሩ ሰዎች (ሠራተኞች) ከሙስና ነፃ እንዲሆኑ ማበረታታትና ጥራት ያለው አገልግሎት ስለመስጠታቸው ማትጊያ ይሆናቸው ዘንድ የሞራልና ቁሳዊ ድጋፍ መስጠት፤
  9. ከሌሎች መሰል አገር በቀል አህጉራዊና አለም አቀፋዊ ማኀበራት ጋር በመስኩ የሥራ ግንኙነትና ትብብር መፍጠር፤
  10. የሙስናን መንስኤዎች በማጥናት የመከላከል ዘዴዎችን መቀየስና ተግባራዊ ማድረግ፤
  11. የግልጽነትና የተጠያቂነት ባህል በህብረተሰቡና በመንግሥት ኃላፊዎች ዘንድ እና ማኀበራዊ ተቋማት መሪዎች እንዲለመዱ ሙሉ ጥረት ማድረግ፡፡
  12. በሀገራችን የሚካሄደውን ምርጫ ነፃ፣ ፍትሀዊ እና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን የበኩሉን ድርሻ በተሻሻለው የኢትዮጵያ የምርጫ ህግ አዋጅ ቁጥር 532/1999 አንቀጽ 89 እና 90 መሠረት ከቦርዱ ፍቃድ ሲያገኝ የሥነ ዜጋና የመራጮች ትምህርት ለመራጮች በመስጠት መሳተፍ ወይም በምርጫ ሕጉ አንቀጽ 78 እና 79 መሠረት ከቦርዱ ፍቃድ ሲያገኝ በምርጫው ወቅት መታዘብና በአንቀጽ 81 መሠረት የትዝብቱን ሪፓርት ለቦርዱ የማቅረብና ይፋ የማድረግ፡
 
Copy right © 2008 Transparency Ethiopia